Ethiopian fake doctor samuel zemichael fake

የዛሬ 35 ዓመት አንድ ሕፃን ከድሃ ቤተሰብ በጋንዲ ሆስፒታል ተወለደ፡፡ ያ ሕፃን ከተቀሩት ኢትዮጵያውያን ሕፃናት የተለየ ችሎታ አልነበረውም፡፡ ቤተሰቦቹ ድሃ ስለነበሩ በእንክብካቤና በቅምጥል አላደገም፡፡ አባቱን አያውቃቸውም፡፡ የአምስት ወር ህፃን ሳለ ነው በሞት የተለዩት፡፡ 
ገና በወጣትነት ዕድሜ የትዳር አጋርን በሞት መነጠቅ ከባድ ፈተና መሆኑን መገመት አያዳግትም፡፡ ልጆቻቸውን የማሳደግና ቤተሰቡን የማስተዳደር ሸክም እናቱ ትከሻ ላይ ወደቀ፡፡  ኑሮና ብቸኝነቱን መቋቋም የከበዳቸው እናቱ፤ ሕፃኑ ሁለት ዓመት ሲሞላው “ከአንድ፣ ሁለት መሆን ሳይሻል አይቀርም” በማለት ባል አገቡ፡፡ አዲሱ ባላቸውም አላሳፈሯቸውም፡፡ ልጆቻቸውን፣ እንደ “እንጀራ አባት” ሳይሆን ከስጋ ልጆቻቸው እኩል ተንከባክበው አሳደጓቸው፡፡ 
ያ ከድሃ ቤተሰብ የተወለደው ሕፃን፤ በእልህ አስጨራሽ ትግልና ጥረት፣ በከፍተኛ የእውቀት ፍቅርና ትጋት ድህነትን ድል ነስቶ፣ ከራሱ አልፎ ለሌሎች ለመትረፍ በቃ፡፡ የድሃ ወንድም እህቶቹ መመኪያና መኩሪያ ሆነ፡፡ በአሁኑ ሰዓት 13 ወላጅ አልባ ህፃናትን እያሳደገ ያስተምራል፡፡ በተለያዩ ችግሮች የተነሳ የከፍተኛ ተቋም ትምህርታቸውን ሊያቋርጡ የደረሱ በርካታ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን በገንዘብ በመደገፍ፣ ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ አድርጓል፡፡ 
ዶ/ር ኢ/ር ሳሙኤል ዘሚካኤል በሙያው መሃንዲስ ነው፡፡ በ1995 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከቴክኖሎጂ ፋኩልቲ የትምህርት ክፍል የመጀመሪያ ዲግሪውን በሲቪል ኢንጂነሪንግ አገኘ፡፡ ሁለተኛ ዲግሪውን በኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂ ማኔጅመንት በ2000 ዓ.ም ከአውስትራሊያ ካምቢራ ዩኒቨርሲቲ፣ ሦስተኛ (ዶክትሬት) ዲግሪውን ደግሞ በአርባን ፕላኒንግ በቅርቡ ከአሜሪካ ሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ መቀበሉንና ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ደግሞ የተባባሪ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ እንደተሰጠው ተናግሯል፡፡ በተጨማሪም “ላይፍ ኮች ኤንድ ሞቲቬሽን ስፒከር” (የሕይወት ጥበብ አሠልጣኝና የሚያነቃቁ ንግግሮች አቅራቢነት) ሥልጠናዎችን በመውሰድ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የመጀመሪያ ዲግሪ (ቢኤ) እንዳለውና በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በመዘዋወር ስለምህንድስና  ትምህርት እንደሚሰጥ ገልጿል፡፡ 
የአዲስ አድማሱ መንግሥቱ አበበ ከዶ/ር ኢ/ር ሳሙኤል ዘሚካኤል ጋር ያደረገውን ቃለ ምልልስ እንድታነቡ ተጋብዛችኋል፡፡

ከዩኒቨርሲቲ እንደተመረቅህ የት ነበር ሥራ የጀመርከው?
በጥሩ ውጤት ስለተመረቅሁ የመጀመሪያው ሥራዬ በዩኒቨርሲቲው ቀርቼ ማስተማር ነበር፡፡ ሁለተኛ ሥራዬ በአዲስ አበባ መስተዳድር የመሬትና ግንባታ ጉዳዮችን ማማከር ነበር፡፡ ዎርልድ ቪዥን በተባለው ግብረ ሰናይ ድርጅት፣ በኢንቨስትመንት ቢሮና በተለያዩ ተቋማትም ሠርቻለሁ፡፡ 
ከመንግሥት ሥራ የለቀከው ለምንድነው?


የመንግሥት ሥራ የለቀኩት በ1998 ዓ.ም ነበር፡፡ ምክንያቴ ደግሞ ሰነፍ ሆኜ ወይም በሌላ ምክንያት ሳይሆን የራሴን ሥራ ለመጀመር ነው፡፡ 
ያኔ ደሞዝህ ስንት ነበር? የጀመርከውስ ሥራ ምን ነበር?
ከቅጥር ስወጣ ደሞዜ 22ሺ ብር ነበር፡፡ ሥራ የለቀኩት፣ ደሞዝ አነሰኝ ብዬ ሳይሆን፣ በቀሰምኩት እውቀት የራሴን ሥራ ለመጀመር አስቤ ነው፡፡  
አፍሪካን ቪዥነሪስ ዴቨሎፕመት ኩባንያን ከጓደኛዬ ጋር በአንድ ሚሊዮን ብር ካፒታል አቋቋምን፡፡ ለሁለት እናቋቁም እንጂ ገንዘቡ የእኔ ነበር፡፡ ይህንን ኩባንያ የመሠረትኩት፣ ራሴን እንደ አፍሪካዊ ባለራዕይ ስለምቆጥር፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ እኔ ካለፍኩ በኋላ የማይቆም (የማይቋረጥ) ኩባንያ እንዲሆን ስለፈለግሁ ነው፡፡ ብዙ ድርጅቶች ባለቤቱ ሲሞት ሕልውናቸው ያቆማል፡፡ የእኔ እንደዚያ እንዲሆን አልፈለግሁም፡፡ 
ኩባንያው ዘመን ተሻጋሪ እንዲሆን ነው የፈለግኸው?
አዎ!

እዚህ በመዲናችን ሂልተን ሆቴል አለ፡፡ በመላው ዓለም በተመሳሳይ ስም የሚጠሩ በርካታ ሂልተን ሆቴሎች አሉ፡፡ ማክዶናልድ፣ በአንድ ሱቅ ነው የጀመረው፡፡ አሁን በመላው ዓለም 36ሺ ቅርንጫፎች አሉት፡፡ ስለዚህ አፍሪካዊ መለያ (ብራንድ) ያለው፣ በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች እየተስፋፋ የሚሄድ፣ አፍሪካውያን የግዙፍ ኩባንያ ባለቤት የመሆን አቅም እንዳላቸው የሚያመለክት ድርጅት እንዲሆን በማሰብ የተቋቋመ ድርጅት ነው፡፡ 
ተሳካልህ ታዲያ? ኩባንያህ አሁን ምን ላይ ደርሷል?
አዎ ተሳክቶልኛል፡፡ ከጠበኩት ፍጥነት በላይ እየተጓዘ ነው፡፡ የቱንም ያህል አድካሚ ቢሆንም ውጤታማ እየሆነ ይገኛል፡፡ እኔ ከተለያዩ ባንኮች ጋር ነው የምሰራው፡፡ መንግስት የቀረፃቸውን አሰሪ ፖሊሲዎች በመጠቀም በስፋት እየተንቀሳቀስኩ ነው፡፡ በነገራችን ላይ በርካታ ብልህ ሰዎች አንድን ስራ ለመስራት ከባንክ ጋር በጥምረት ይሰራሉ፡፡ እኔም ይንንን የስኬታማ ሰዎች መርህን ነው የምከተለው፡፡ ለምሳሌ በአገራችን ኢኮኖሚ ትልቁን ሚና እየተጫወተ የሚገኘው ደርባን ሲሚንቶ ከ360 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጥቶበታል፡፡ ከዚህ ውስጥ ባለሀብቱ ያወጡት 60 ሚሊዮን ዶላሩን ሲሆን ቀሪውን Cardinal ሚሊዮን ዶላር ግን ከአፍሪካ ልማት ባንክ እና ከሌላ የፋይናንስ ተቋም ነው ያገኙት፡፡ እንደሚታወቀው ባለቤቱ የአለማችን ቢሊየነር ናቸው፡፡ ግን ይህንን የብልሆች መርህ ይከተላሉ እንጂ ያላቸውን ገንዘብ ሁሉ አንድ ፕሮጀክት ላይ አላዋሉም፡፡ እኔም እንደ አቅሚቲ የተከተልኩት ይህንን አለም አቀፍ የኢንተርፕረነሮች መርህን ነው፡፡ 
የዚሁ ኩባንያ አካል የሆነ የአፍሪካ ቪአይፒ (VIP) ክበብ ከጐረቤታችን ኤርትራና ከሰሜን አፍሪካዊቷ ሞሮኮ በስተቀር በተቀሩት የአፍሪካ አገራትና በአገራችን ዩኒቨርሲቲዎች ተመስርቶ በራሳቸው የሚተማመኑ፣ ቀና አስተሳሰብ ያላቸው ባለራዕይ የዩኒቨርሲቲ ተማሪችንና መምህራንን እያፈራ ይገኛል፡፡ 
አፍሪካ ቪዝነሪስ ዴቨሎፕመንት ካምፓኒ ምንድነው የሚሠራው?
ይህ ድርጅት በዋናነት ተግባሩ፣ የኮንስትራክሽን ሥራ ይሰራል፡፡ ኮፊ ላንድ ኮፊ የተሠኘ የወጪና ገቢ ንግድ ድርጅታችን፣ የኢትዮጵያን ቡና ወደ ውጭ ይልካል፡፡ ቀደም ሲል ከሌሎች አጋሮች ጋር በኢቴቪ “ባለ ራዕይ” የሚል ቶክሾው ነበረን፡፡ የሚዲያና የሞቲቬሽን ሥራዎች እንሠራለን፣ የአስጐብኚ ድርጅት አለን፡፡ ከሕንድ ኩባንያ ጋር በጆይንት ቬንቸር ጣና ሐይቅ ላይ የሪዞርት ሥራ ጀምረናል፤ በሀዋሳ ሐይቅ ላይም ሪዞርት ለመሥራት ከሚመለከታቸው ኃላፊዎች ጋር በመነጋገር የቦታ ጥናት እያደረግን ነው፡፡ 
ዴቨሎፕመንት ኢንስቲቲዩቱም ለተለያዩ ግለሰቦችና ድርጅቶች ሥልጠና ይሰጣል፡፡ ሥልጠናው በአብዛኛው በት/ቤት ከሚሰጠው የአካዳሚክ ሥልጠና የተለየ ነው፡፡ አንድ ሰው በዙሪያው ያለውንና በውስጡ የሚገኘውን እምቅ ችሎታና ኃይል እንዲያውቅ፤ እንዲፈትሽ፣ እንዲያይ፣ በውስጡ ያለውን መክሊት አውጥቶ በሚገባ እንዲጠቀም የሚያደርግ፣ ሥልጠና ነው፡፡ በአጠቃላይ አንድ ሰው ከራሱ አልፎ ለሌላው መትረፍ እንደሚችል የሚያግዙትን ሥልጠናዎች እንሰጣለን፡፡ 
ፍርሃታችንን እንዴት እንገራለን?

የሚለው ከማኔጅመንት ሥልጠናዎች አንዱ ነው፡፡ አንዳንድ ሰው የራሱን ሥራ ለመሥራት ወስኖ ሲያበቃ፣ ያለውን ገንዘብ አውጥቶ ቢዝነስ ለመጀመር ይሰጋል፡፡ ሌላው ትዳር ለመያዝ ይፈራል፣ የተለያዩ የፍርሃት መንገዶች አሉ፡፡ ፍርሃት በተወሰነ ደረጃ ሲሆን መጥፎ አይደለም፤ ለጥንቃቄ ይረዳል፡፡ ከልክ ሲያልፍ ግን፣ እጅና እግር አሳስሮና ሽባ አድርጐ ያስቀምጣል፤ በድህነትና በችግር ታስረን እንድንኖር ያደርጋል፡፡ ይህንን ዓይነቱን  ፍርሃት የሚያስወግድ ሥልጠና እንሰጣለን፡፡  
ሁለተኛው ሥልጠና ሥራ ፈጠራ ወይም ኢንተርፕሪነርሺፕ ነው፡፡ ይህ ሐሳብ ብዙ ጊዜ ለበርካታ ሰዎች ግልጽ አይደለም፡፡ ሥራ መፍጠር ማለት በዙሪያችን ያሉትን ችግሮች መቅረፍ ማለት ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች ገንዘብ አላቸው፡፡ ነገር ግን ገንዘባቸውን እንዴት በአግባቡ መጠቀም እንዳለባቸው አያውቁም፡፡ እኛ ችግራቸውን ተገንዝበን መፍትሔውን ከፈጠርንላቸውና ካሳየናቸው በገንዘባቸው ይገዙናል፤ እኛም በገንዘቡ እንጠቀማለን፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ችግር አለ ወይ?

አዎ በሽበሽ ነው፤ ሞልቷል፡፡ ሥራ ለመፍጠር ዕድሎች አሉ ወይ? አዎ በጣም ሞልተዋል፡፡ ሥራ መፍጠር ማለት ይህ ነው፡፡ 
በነገራችን ላይ ትልልቅ ሕልም ያላቸው ሰዎች፣ ችግሮችን ከማማረር ይልቅ አንዳች ፈታኝ ሁኔታ ሲያጋጥማቸው መፍትሔውን ወደመፈለግ ይሄዳሉ፡፡ ይህም አዲስና ሌላ ተጨማሪ የስራ እድል ይፈጥርላቸዋል፡፡ የትኛውም የሥራ ፈጠራና መፍትሔ የሚመነጨው ከችግር ነው፡፡ እያንዳንዱ ሰው፣ ወደዚህች ዓለም ሲመጣ፣ ችግር መፍቻ መክሊት ወይም መፍትሔ ይዞ ነው የሚመጣው፡፡ 
ቢል ጌት እንኳን ተወለደ – እሱ በመወለዱ የማይክሮሶፍት ሶፍትዌርን ማግኘት ቻልን!
ስቲቭ ጆብስ እንኳን ተወለደ – እሱ በመወለዱ የአይፎንን ምርቶች ማግኘት ችለናል!


ኼነሪ ፎርድ እንኳን ተወለደ – የሰውን ድካም የሚቀንስ መኪና ፈጥሯልና!
የራይት ብራዘርስ ወንድማማቾች እንኳን ተወለዱ – የእነሱ መምጣት፣ ከአንዱ የዓለም ጥግ ወደ ሌላው የምናደርገውን ጉዞ አሳጥሮልናልና!
የሕክምና የፈጠራ ሰዎች እንኳን ተወለዱ – በእነሱ መወለድ፣ ብዙ ሰዎች ከሕመምና ስቃይ ፈውስ አግኝተዋልና!
አንተ እንኳን ተወለድክ – ሰዎችን የሚያነቃቁ መረጃዎችን በጋዜጣችሁ በማውጣት፣ እኔን ጨምሮ ብዙ ሰዎች ቅዳሜ ቅዳሜ አዲስ አድማስን በናፍቆት እንድንጠብቅ አድርገሃልና!…
እኔ የቱንም ያህል ብማር፣ ከማውቀው ይልቅ የማላውቀው፣ ከደረስኩበት ይልቅ ያልደረስኩበት፣ ከገባኝና ከተረዳሁት ይልቅ ያልገባኝ ይበልጣል፡፡ ምናልባት ኢንጂነር የሚለው ማዕረግ አብሮኝ ስላለ፣ አንዳንዶች ያወቅሁ፣ የተረዳሁ የጨረስኩ ሊመስላቸው ይችላል፡፡ የኢንጂነሪንግ ትምህርት 104 ዘርፎች አሉት፡፡ ቴክስታይል፣ ሌዘር፣ ኬሚካል፣ ዎተር፣ ረዚደንስ፣ ኃይዌይ ወዘተ…ኢንጂነሪንግ የተባሉ ብዙ ዘርፎች አሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ እኔ የማውቀው አንዱን ቁንፅል ዘርፍ ነው – ሲቪል ኢንጂሪንግን፡፡ 
የበለጠ ለማወቅ ብዙ መረጃዎች መሰብሰብና ማንበብ አለብኝ፡፡ ስለዚህ የእናንተንም ጋዜጣ አነብባለሁ፣ ምክንያቱም አንተ የምታቀርበው የስኬታማ ሰዎች ታሪክ በጣም ያነቃቃኛል፡፡ በዩኒቨርሲቲ ቆይታችን በመጀመሪያ፣ በሁለተኛና በሦስተኛ ዲግሪ ትምህርታችን የምንቀስመው እውቀት 20 በመቶ ነው፡፡ ቀሪውን እውቀት የምንማረው ከሌላ የሕይወት መስክ ነው፡፡ ት/ቤት ገብቶ መማር ጥሩ ነው፡፡ ግን በቂ አይደለም፡፡ ሁል ጊዜ ባለን ላይ መጨመርና ዘወትር ራስን ከዘመኑ እውቀት ጋር ማስማማት (አፕዴት ማድረግ) ያስፈልጋል፡፡ ሙሉ ሰው መሆን የምትችለው ያኔ ነው፡፡ አንተም እንኳን ተወለድክ ያልኩት፣ ሙሉ ሰው ለመሆን ስለረዳኸኝ ነው፡፡ 
ሥራ እንድንፈጥር የሚያደርገን ቀና አስተሳሰብ (ፖዘቲቭ ቲንኪንግ) ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች “ኢትዮጵያ ውስጥ ከምወለድ፣ አሜሪካ ውስጥ እንስሳ፣ ዛፍ፣…ሆኜ ብወለድ ይሻል ነበር፡፡ እዚያ እንስሳው ይከበራል፣ ዛፉም እንክብካቤ ያገኛል፡፡ እዚህ ግን…” በማለት ያማርራሉ፡፡ እዚህ ያለውን እውነት መቀበል ይቸግራቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ አብዛኛው ሰው ከመንግስት ይጠብቃል፡፡ ለእኔ ከመንግስት በፊት የሚቀርበኝ አንድ ሰው አለ፡፡ ያም ሰው እኔ ነኝ፡፡ ቀና አስተሳሰብ የምንለው እንዲህ ዓይነት አመለካከት እንዲኖረን የሚያደርግ ነው፡፡ 
ብዙ ሰው ራዕይ (ቪዥን) የለውም፡፡ ከአምስት ዓመት በኋላ የት እንደሚደርስ አያውቅም፡፡ የዛሬ ዓመት ምን ያህል ገቢ እንደሚኖረው አይረዳም፡፡ ዝም ብሎ በዘልማድ እየኖረ ይመሻል ይነጋል፡፡ የብዙዎቹ ኑሮ ተመሳሳይ ነው፡፡ ለአቅመ አዳም ወይም ለአቅመ ሔዋን መድረስ፣ ከዚያም ማግባት፣ የተገኘውን መስራት፣ ልጅ መውለድ፣ ሲሞቱ በዕድርተኞች ተሸኝቶ መቀበር ነው፡፡ ብዙ መስራትና ታሪክ መፍጠር እየቻለ የዚህ ዓይነት ተራ ህይወት ኖሮ እስከወዲያኛው የሚያሸልበው ሰው በርካታ ነው፡፡ እኔ ሳልፍ ግን ዕድር አያስፈልገኝም፡፡ ምክንያቱም በመሰረትኳቸው ድርጅቶች ውስጥ የተቀጠሩ ብዙ ሺ ሰራተኞች ወጥተው ይሸኙኛል፡፡ የማከናውናቸው ስራዎችም ብዙ አድናቂዎችና ወዳጆች ስለሚፈጥሩልኝ ወደ ማይቀረው ቤቴ የማደርገው ጉዞ አያሳስበኝም፡፡ 
አንዳንድ ሰዎች ሺ ዓመት ላልኖር ምን ያስጨንቀኛል?

ይላሉ፡፡ ግን ከፈለጉ መኖር ይችላሉ፡፡ የምርጫ ጉዳይ ነው፡፡ ላሊበላ ለብዙ መቶ ዓመታት እየኖረ ነው፡፡ ንጉሥ ላሊበላ በሌለበት ዘመን እኛ ስለላሊበላ እያወራን ነው፡፡ አክሱማውያን ስላቆሙት ሐውልት አሁንም እያወራን ነው፡፡ ስለውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ ስለአብርሃ ወአፅብሃ፣ ስለሶፍ ዑመር፣ ዛሬም ይወራል፡፡ እነዚህን ድንቅ የስልጣኔ ናሙናዎች የሰሩ ጠበብቶች ስማቸው ከመቃብር በላይ እየተነሳ ነው፡፡ ለእኔ ሺ ዓመት መኖር ማለት ይሔ ነው፡፡ እንግዲህ ሺ ዓመት መኖርን የሚያስቡ ዜጎችን ለመፍጠር ነው 52 ሥልጠናዎችን የምንሰጠው፡፡  
በሚዲያና በምንሰጣቸው ስልጠናዎች የሰው አእምሮ በመለወጥ፤ ስራ ወዳድና ባለራዕይ፣ ባለፈጠራና ቅን አሳቢ … ለመሆን የሚረዱ መጻህፍት ከውጭ እያስመጣን ለዩኒቨርሲቲዎችና ለተለያዩ ድርጅቶች እናከፋፍላለን፡፡ 
ከዚህ ውጭ በአስጎብኚ (ቱር ኤንድ ኦፕሬተር) ዘርፍ፣ ቱሪስቶችን እጅግ ዘመናዊ በሆኑ ስምንት ቪ 8 መኪኖችና በስድስት ቫን መኪኖች፣ ወደተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች በመውሰድ እናስጎበኛለን፡፡ በግንባታ ዘርፍም ለምንሰጠው አገልግሎት የሚውሉ የተለያዩ መሳሪያዎችና መኪኖች አሉን፡፡ 
በምትሰጠው የማነቃቂያ (ሞቲቬሽን) ሥልጠናና በምታደርገው ንግግር የሰው አቀባበል እንዴት ነው?
እኔ የምሰጣቸው ስልጠናዎች፤ ሰዎች በሚገጥማቸው ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ተስፋ እንዳይቆርጡ፣ ሌላ የተሻለ ቀን ከፊታቸው እንዳለ እንዲያስቡ፣ የሚያውቋቸው ትልልቅ ስኬታማ ሰዎች ሁሉ እነሱ በነበሩበት ሁኔታ ውስጥ እንዳለፉ፣ እነዚያ ስኬታማ ሰዎች ከእነሱ የሚለዩት፣ ተስፋ የሚያስቆርጡ ነገሮችን ተስፋ በማስቆረጥ፣ ጨክነው በመሻገራቸው ውጤታማ እንደሆኑ … እንዲያውቁ ነው የማደርገው፡፡ 
ለምሳሌ፤ ዛሬ እኔ የደረስኩበትን በማየት አንዳንድ ተማሪዎቼ እንደ እድለኛ ሊቆጥሩኝ ይችሉ ይሆናል፡፡ በእርግጥም ዕድለኛ ነኝ፡፡ ሆኖም ግን የእኔ ዕድለኛነት ከእነሱ የተለየ አይደለም፡፡ አቃቂ ከተማ ውስጥ በፈረስ ጋሪ የጠዋት ተማሪ ስሆን ከሰዓት፣ የከሠዓት ተማሪ ስሆን ጠዋት እየሰራሁ ነው የተማርኩት፡፡ ሰው ቤት በእረኝነት ተቀጥሬ ከብቶች እየጠበቅሁና እያጠብኩ፣ አዛባቸውን እየጠረግሁ አበሳ አይቼ ነው የተማርኩት፡፡ በማገኘው ገንዘብ መጻሕፍት እገዛለሁ፣ ማንበብ ያለብኝን አነብባለሁ፡፡ እንዲህ አይነት አስቸጋሪ ፈተናዎች፣ በፅናት ተቋቁሜ በማለፍ ነው ዛሬ ለደረስኩበት ደረጃ የበቃሁት፡፡ ሰው ቤት በእረኛነት ተቀጥረህ እየሰራህ የ12ኛ ክፍልን መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና መውሰድ ይከብዳል፡፡ ነገር ግን የተሻለ ጊዜ ማየት ከፈለግህና ጎዳና ላይ ከመውደቅ እነዚያን አስቸጋሪ የሆኑትን ስራዎች በማከናወን ነገ የበለጠ አስቸጋሪ የሚሆነውን ጊዜ ልትሻገር የምትችልበትን ዕድል ትፈጥራለህ፡፡ 
አንድ የፈረንጆች አባባል አለ፡፡ Opportunity Plus Preparation = Luck፡፡ ዝግጁነትና አጋጣሚ ሲደመሩ ነው ዕድል የሚባለው፡፡ በዚህ ቀመር መሰረት፣ ሁሉም ሰው ዕድለኛ ነው፡፡ ሥራን ሳይንቅ ለመስራት ዝግጁ ከሆነ የማያሸንፍበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ 
የቀድሞውን የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት የክቡር ግርማ ወ/ጊዮርጊስን የሕይወት ታሪክ በአማርኛና በእንግሊዝኛ አዘጋጅቼ እየተጠናቀቀ ነው፡፡ የእሳቸውን ታሪክ አንዳንድ ሰዎች ያውቃሉ ብዬ እገምታለሁ፡፡ በጣም የሚገርም ታሪክ አላቸው፡፡ 12 ዓመት የቆዩበት ኢዮቤልዩ ቤተመንግስት ሲሰራ፣ በቀን ሰራተኛነት ተቀጥረው 1.50 ማሪያ ትሬዛ እየተከፈላቸው ድንጋይ አንጥፈዋል፤ አሸዋ አቡክተዋል፡፡ ከራሳቸው አንደበት ነው የሰማሁት፡፡ ሸቀጣ ሸቀጥ ነግደዋል፣ ከገጠር ዕንቁላል እየገዙ ከተማ አምጥተው ሸጠዋል፣ አንድ ወር ጨለማ ቤት ታስረው ያውቃሉ፡፡ በአንድ ወቅት ጦር ፍርድ ቤት ቀርበው ለሞት አንድ እርምጃ ሲቀራቸው ነው የተረፉት፡፡ እኚህ የፅናት ምሳሌ የሆኑ ሰው፤ የጥቁሮች የነፃነት ዓርማ እንደሆነች የሚነገርላትና የሰው ልጅ መገኛ የሆነች አገር ርዕሰ ብሄር መሆን የቻሉት፣ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮችና ውጣ ውረዶች አልፈው ነው፡፡ 
እንደሳቸው ያሉ ሰዎችን የሕይወት ታሪክ ከሰማህና ካነበብክ አንተም ተመሳሳይ ችግር ሲመጣብህ፣ የእነሱ ገጠመኝ ትዝ ይልሃል፡፡ ምን ዓይነት አቅም ይሰጥሃል መሰለህ!

ተስፋ ቆርጠህ ለየትኛው ጊዜዬ ነው? ብለህ እርግፍ አድርገህ እንዳትተው ያደርግሃል፡፡ ከጨከንክና መከፈል ያለበትን ዋጋ ከከፈልክ ነገ ወደተሻለ ነገር ታልፋለህ፡፡ ይህንን ነው ታሪካቸው የሚናገረው፡፡ ብዙ ትንንሽ ሰዎች’ኮ ናቸው ትልልቅ የሆኑት፡፡ ከእናቱ ማኅፀን ሀብትን፣ እውቀትን ዝናን… ይዞ የመጣ ሰው የለም፡፡ 
ብዙ የሚያነቃቁ መጻሕፍት ተተርጉመው ገበያ ላይ ውለዋል፡፡ እነዚያን መጻሕፍት የሚያነቡ ሰዎች እምብዛም ሲለወጡ አይታዩም፡፡ ለምን ይሆን? ከአተረጓጎም ስህተት ነው ወይስ ሌላ ምክንያት አለ?
ለዚህ ጥያቄ ብዙ መልሶች አሉ፡፡ መጻህፍቱን አንብበው ለመለወጥ የሚያቅዱ ሰዎች ለእቅዳቸው ታማኝ አይደሉም፡፡ ጠዋት በ12 ሰዓት ብትመጣ እኔን ቢሮ ታገኘኛለህ፣ ማታ በ5 ሰዓት በዚህ ስታልፍ ብታየኝ አለሁ፡፡ የጻፍኩትን መጽሐፍ እኖራለሁ፣ የምኖረውን ነገር እጽፋለሁ፡፡ የስኬት መፃህፍትን የማነበው “ጎበዝ እንባቢ ነው…” ለመባል ሳይሆን፣ ያነበብኩትን በቀጥታ ለመተግበር ነው፡፡ ሁሌም ያነበብኩትን በተግባር እኖረዋለሁ፡፡ ስለዚህ መጻሕፍት ይጠቅሙኛል ማለት ነው፡፡ 
አንድ ሰው ማለት፣ የተማረው ትምህርት፣ ያነበባቸው መፃህፍት፣ ከሰው ታሪኮች የቀሰማቸው እውቀቶች… ድምር ውጤት ነው፡፡ አንዳንድ ግነት የሚበዛባቸው መጽሐፍት እንዳሉ ይገባኛል፡፡ ጥቂት መጻሕፍት ሲተረጎሙ፣ የእንግሊዝኛውን ትርጉም በትክክል ላያስተላልፉ ይችሉ ይሆናል፡፡ ነገር ግን አብዛኞቹ የተጻፈላቸውን ዓላማና ግብ እንዲመቱ ተደርገው ነው የሚቀርቡት፡፡ ችግሩ ዘርፈ ብዙ ቢሆንም ዋናው ግን የተፃፉትን መጻሕፍት ካነበቡ በኋላ፣ ወደ ህይወት ለመተርጎም አለመድፈር፣ አለመቁረጥ፣ አለመጨከን ነው፡፡ ብዙ ሰው ሀብታም መሆን ይፈልጋል፡፡ ነገር ግን ሀብታሞች የሚከተሉትን የአኗኗር መርህ ለመከተል ፈቃደኛ አይደለም፡፡ 
የሀብታሞች መርህ ምንድነው?
ብዙ ናቸው፤ ዋነኛው ግን ቁጠባ ነው፡፡ ትንሽ ገንዘብ ሲያገኝ ለዚህም ለዚያም እየጋበዘ ካባከነ፣ ትንሽ ሳንቲም ሲይዝ ሁሉ እያማረው ካጠፋ፣ እንዴት ነው ሀብታም የሚሆነው?

መቆጠብና ማጠራቀም ያስፈልጋል፡፡ አቅሙ በሚኖርበት ጊዜ በዓለማችን አለ በሚባለው ሪዞርት ውስጥ ለአንድ ሌሊት ሺ ዶላሮች ከፍለህ ማደር ትችላለህ፡፡ ለሁሉም ጊዜ አለው፡፡ ገበሬውን ብታየው ይሞታታል እንጂ ለዘር ያስቀመጠውን እህል አይበላም፡፡ መነሻ ካፒታል ማለት ዘር ነው፡፡ ብዙ ሰዎች መነሻ የሚሆናቸውን ካፒታል ያገኙና ያጠፉታል፡፡ አንዳንዱ ፍቅረኛውን ለማስደሰት ሲል በይሉኝታ ያባክናል፣ አንዳንዱ ከልማዳዊ የኑሮ ዑደት ጋር በተያያዘ ለ40፣ ለ80፣ ለሙት ዓመት፣ ለሰርግ፣… ሊያውለው ይችላል፡፡ ልማዳዊ ባህል እንደሆነ ይገባኛል፡፡ ሟችን ሲሸኙ ድሆችን መርዳት ያለ ቢሆንም፣ ያለውን ሁሉ አውጥቶ ማባከን የሃይማኖቱ ትምህርት እራሱ የማይደግፍ መሆኑን አባቶች ሲናገሩ እየሰማን ነው፡፡ እነዚህ ልማዳዊ ድርጊቶች ያለንን ጥሪት አሟጠን እንድናጠፋ፣ ጊዜያችንን እንድናባክን ያደርጉናል፡፡ 
ሌላው ችግር ብዙ ሰው በትንሽ ነገር ይረካል፡፡ በትንሽ ነገር መርካት አያስፈልግም፡፡ እኔ በትንሽ ነገር አልረካም፡፡ ብልጽግና፣ ትልቅነት፣ አሸናፊነት ይገባኛል፡፡ በዓላማ ነው ወደዚች ዓለም የመጣሁት፡፡ ከራሴ አልፌ ለሌሎች መትረፍ ይገባኛል… ብዬ ውስጤን አሳምኜዋለሁ፡፡ የእኔ ወላጆች እንዲህ አምነው ቢሰሩ ኖሮ፣ ያሳለፍኩት ውጣ ውረድ አይገጥመኝም ነበር፡፡ በእኔ የትውልድ ሃረግ፣ ከአሁን በኋላ ድህነት እንደማይኖር እርግጠኛ ነኝ፡፡ አንደኛ ልጆች ስወልድ አባካኝ እንዳይሆኑና የስራ ሰው እንዲሆኑ ኮትኩቼ ነው የማሳድገው፡፡ ሁለተኛ፤ አባት ያቆየላቸውንና ሕይወታቸውን የሚለውጡበት ዘር ወይም እርሾ ያገኛሉ፡፡ የብዙዎቹ ሰዎች ችግር ይህንን አለማግኘት ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ 
አዋዋልም ወሳኝ ነው፡፡ የአገሬ ሰዎች “አዋዋልህን ንገረኝና ማንነትህን እነግርሃለሁ” የሚል አባባል አላቸው፡፡ እኔ ሕይወትን በትግል ካሸነፉ ሰዎች ጋር እንጂ አሉታዊ አስተሳሰብ ካላቸው ሰዎች ጋር አልውልም፡፡ ምክንያቱም እምነቴን፣ ራዕዬንና ዕቅዴን እንዲያበላሹብኝ አልፈልግም፡፡ ሰው ውሎውን ነው የሚመስለው፡፡ እኔ የምውላቸው ሰዎች በአንድ የልብስ ስፌት መኪና ተነስተው ከ3ሺ ሰራተኛ በላይ መቅጠር ከቻሉ የጋርመንት፣ ሪልእስቴትና የሆቴል ባለቤቶች ጋር ነው፡፡ ከጣራ ጠጋኝነትና ከቀለም ቀቢነት ተነስተው ለ6,200 ዜጎች የስራ እድል መፍጠር ከቻሉ ሰው ጋር ነው የምውለው፡፡ ድሮ አንድ ጫማ እንደቡታጋዝ ክሮቹን እየቀየሩ ሶስት ዓመት ያደርጉ የነበሩ ሰው፣ በሚሊዮን ብሮች አምረው በተሰሩ ቤቶች ውስጥ ከሚኖሩ፣ ሶስትና አራት ሚሊዮን ብር ታክስ የሚከፈልባቸው መኪኖች ከሚያሽከረክሩ ሰዎች ጋር ነው የምውለው፡፡ አብሬአቸው ስውል የየዕለቱን የስራ ዲሲፒሊን፣ የገንዘብ አጠቃቀማቸውን፣ የሰራተኛ አያያዛቸውን፤… ዩኒቨርሲቲ ከምማረው በላይ ከእነሱ በቀጥታ የምቀስመው ነገር አለ ማለት ነው፡፡
እነዚህ ሰዎች ዛሬም ድረስ ተግተው የሚሰሩት ራዕያቸውን ለማስፈጸም እንጂ ለምግባቸውና ለልብሳቸው አይደለም፤ ለዚያማ ያላቸው በቂ ነው፡፡ ነገር ግን እንቅልፍ የማያስወስድ ራዕይ አላቸው፡፡ ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች የመትረፍ ሕልም አላቸው፡፡ ይህ ራዕይ፣ የእኔም ራዕይ ነው፡፡ ለእንጀራና ለምግብ ቢሆን፣ ስራ ለቅቄ ስወጣ የወር ደሞዜ 22ሺ ብር ነበር፡፡ እኔን በምቾት ለማኖር በቂ ነበር፡፡ ከስራ ስወጣ የከፈልኩት ዋጋ አለ፡፡ የተሰጠኝ መኪና ነበረኝ፤ ያንን ትቼ ታክሲ መጋፋት ጀመርኩ፣ ዝናብ ደብድቦኝ እቤት ስገባ ራዕዬ ያልታያቸው፣ ህልሜ ያልገባቸው እናት፣ እህትና ጉረቤቶቼ “እሰይ ይበልህ!

ድሎት አስጠልቶህ የመረጥከው ሕይወት ነው፤…” ይሉኝ ነበር፡፡ ያኔ “ተሳሳትኩ እንዴ? ተመልሼ ልግባ?” የሚል ሃሳብ አልመጣልኝም ግን በውስጥህ የሚንቦገቦገው ህልም፣ ከፊት ለፊትህ የታየህን ራዕይ ለመጨበጥ እንድትቆርጥ፣ እንድትጨክን ያደርግሃል፡፡ 
ራዕይ እንዴት ይገለፃል?
ራዕይ ለሌሎች የማይታይ ነገር ማየት ማለት ነው፡፡ አዎ ለሌሎች የማይታየው ላንተ ቁልጭ ብሎ ይታይሃል፡፡ 
ኼነሪ ፎርድ፤ ዘመዶቹ፣ አክስት፣ አጎትና ጎረቤቶቹ፣…. በቅሎ፣ ፈረስ፣ አህያ… ሲጠቀሙ እሱ ዘመዶቹ ያልታያቸው መኪና ነበር የታየው፡፡ ይህ ነው ራዕይ፤ ሌሎች አይቻልም ያሉትን ይቻላል ብሎ ማድረግ፣ ሌሎች አይቻልም ብለው ፈርተው ያፈገፈጉበትን ይቻላል ማለት፣ ደፍሮ መግባት… ማለት ነው ራዕይ፡፡ 
ራዕይን በተመለከተ እኔ የምጠቀምበት አንድ መርህ አለኝ “ራዕይ ማለት የሚታትሩለት ብቻ ሳይሆን አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የሚሞቱለት ጭምር ነው” የሚል፡፡ ልትሞትለት የተዘጋጀህለትን ራዕይ ለማሳካት እንቅልፍ ብታጣ ትልቅ ነገር አይደለም፡፡ ምክንያቱም ልትሞትለት’ኮ ተዘጋጅተሃል፡፡ ለመሞት የተዘጋጀህለትን ለማሳካት በምታደርገው እንቅስቃሴ ውስጥ የሚገጥምህ ውጣ ውረድ ከሞት ስለማይበልጥ፣ ችግሮቹን መቋቋምና መጋፈጥ አይከብድም፡፡ 
ራዕይን ለማሳካት መንገዱ ሁሉ አልጋ በአልጋ አይደለም፡፡ ሕይወት ራሱ’ኮ ያስተምረናል፡፡ ስንወለድ በእናታችን እቅፍ ውስጥ ነበርን፡፡ ከዚያ ዳዴ ማለት ብንጀምርም ወዲያው መራመድ አልቻልንም፡፡ ጠረጴዛ ይዘን እየወደቅንና እየተነሳን ደግሞ እየቆምን፣ የእናትን እጅ ይዘን እየተራመድንና እየወደቅን፣ በኋላ ደግሞ እየጠነከርን፣ ….

ነው ያደግነው፡፡ እኔ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የማውቃቸው ስኬታማ ትልልቅ ሰዎች በሙሉ ያልወደቁ አይደሉም፤ ወድቀው የተነሱ ናቸው፡፡ ያልተፈተኑ አይደሉም፤ እንደወርቅ በእሳት ውስጥ አልፈው ተፈትነው ነጥረው የወጡ ናቸው፡፡ እጅህ ላይ ያለውን ወርቅ፤ “ምን ሆነህ ነው እንዲህ ያማረብህ? ዋጋህስ ከሌሎች ማእድናት ውድ የሆነው ለምንድነው?” ብለህ ብትጠይቀው “በእሳት ውስጥ ተፈትኜ ስላለፍኩ ነው” ይልሃል፡፡ በፈተና ውስጥ ማለፍ ዋጋ ይጨምራል ማለት ነው፡፡ 
ራዕይህን እንዳታሳካ አንዳንድ ነገሮች ሊያዘገዩህ ይችላሉ፡፡ የተወሰነ ወቅት ላይ ለስራ የማያመቹ ፖሊሲዎች፣ የብድር ማጣት፣ ሰው ሰራሽ አደጋዎች፣ የፋይናንስ እጥረት… ሊያዘገዩህ ይችላሉ፡፡ ወዲው መፍትሄ ስለምትፈልግለት ከግብህ ግን ሊያስቀሩህ አይችሉም፡፡ ይህንን ነገር ነው እንግዲህ ለተማሪዎቻችን የምንነግረው፡፡ ባለፉት ሶስት ዓመታት ውስጥ ከ32 ዩኒቨርሲቲዎች በ27ቱ ከአንድ እስከ ሶስት ሳምንታት፣ ለዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች፣ ለመምህራን፣ ለአስተዳደር ሰራተኞችና ለተማሪዎች ያለምንም ክፍያ ሥልጠና ሰጥቻለሁ፡፡ እውቀቴን በጂዲፒ ፕሮግራሙ በማካፈል፣ የዜግነት ድርሻዬን በመወጣት ጥሩ ምሳሌ መሆን እፈልጋለሁ፡፡ ለምሳሌ በአሁኑ ሰዓት ኬንያ በሚገኘው ናይሮቢ ናሽናል ኤይር ወይስ አምስት መቶ አርባ ሺህ ብር ከፍዬ የፓይለቲንግ ትምህርት እየተማርኩ ነው፡፡ ሳጠናቀቅ የግል ጀት የማብረሪያ ላይሰንስ (ፈቃድ) ይኖረኛል፡፡ በቀጣይም የግል ጀት እንደሚኖረኝ አምናለሁ፡፡ አየህ በዚህ ሁሉ ለተማሪዎቼ ምሳሌ ለመሆን እየጣርኩ ነው፡፡ 
በዚህ ስልጠና አንዳንድ ፈታኝ ሁኔታዎች ገጥሟቸው ትምህርታቸው ሊያቋርጡ የደረሱ ተማሪች፣ ለካንስ እንዲህ ነው ወይ?

ብለው ጨክነው እንዲማሩ ያደርጋቸዋል፡፡  በዚህ አይነት በየዩኒቨርሲቲዎቹ የአፍሪካ ቪአይፒ ክለብ አቋቁሜአለሁ፡፡ ይኼ የአፍሪካ ባለራዕዮች ክለብ ነው፡፡ በሚቀጥሉት 10 ዓመታት አንድ ሚሊዮን የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ለማፍራት እየሰራሁ ነው፡፡ 
ተማሪዎቼ ራሳቸውን በጣም አስፈላጊ ሰው አድርገው ነው የሚቆጥሩት፡፡ ከተመረቁ በኋላ እንደ ሰንሻይን ኮንስትራክሽን ባለቤት እንደ አቶ ሳሙኤል 6,200 ሰራተኞች፣ እንደግሪን ኮፊ ባለቤት እንደ አቶ ታደለ አብርሃ 13ሺ ሰራተኞች፣ እንደ ኖክ ኩባንያ ስራ አስፈፃሚ እንደ አቶ ታደሰ ካሳና በአጋሮቻቸው እንደተቋቋመው የንግድ ድርጅት 15ሺ ሠራተኛ… መቅጠር ባይችሉም፣ እያንዳንዳቸው 100 ሰው መቅጠር ቢችሉ፣ ከ19 ዓመት በኋላ የእኔ ተማሪዎች ለ70 ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ፡፡ ስለዚህ፣ አሁን ወገኖቼ ወደ ሱዳን የሚሰደዱባቸው መንገዶች፣ ሌሎች በመኪኖች ተሳፍረው ለስራ ፍለጋ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡባቸው ጎዳናዎች ይሆናሉ፡፡ ይህ ነው ራዕይና ግቤ፡፡ ይህ ምኞች ሳይሆን ራዕይ ነው፡፡ በምኞትና በራዕይ መካከል ትልቅ ልዩነት አለ፡፡ ራዕይ የሚታይና የሚጨበጥ እውነት ነው፡፡ 
አፍሪካ ቪዥነሪስ ዴቨሎፕመንት ካምፓኒ በአሁኑ ወቅት ለ144 ቋሚ ሰራተኞች ለ 122 ጊዜያዊ ሰራተኞች በአጠቃላይ ለ 246 ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል፡፡ ካፒታሉም ወደ መቶ ሚሊየን ብር እየተጠጋ ይገኛል፡፡ በቀጣይም በሌሎች ዘርፎች ለመሰማራት እየተንቀሳቀስን እንገኛለን፡፡
ዶ/ር ኢ/ር ሳሙኤል ለዛሬው ማንነቱ ያበቁት ሰዎች ባለውለታዬ ናቸው ይላል፡፡ የመጀመሪያዋ ድሃም ቢሆኑ ከልጅነት አንስቶ ጥሩ ሰብእና እንዲኖረው በስነ ምግባር ቀርፀው ያሳደጉትን እናቱን ወ/ሮ እኔቱ ወርቅነህ ናቸው፡፡ የእንጀራ ልጅ ነው ሳይሉ እንደወለዱት ልጅ ያሳደጉትን 12ኛ ክፍል ወድቆ ዝዋይ ሄዶ ሲማር ከፍተኛ ድጋፍ ያደረጉለትን ለአባቱ ለአቶ ዘሚካኤል ኃ/ኢየሱስ ከፍተኛ አክብሮት እንዳለው ገልጿል፡፡ በሮል ሞዴልነት ለቀረፀው ለኢ/ር ኤርሚያስ አሰፋና ነገሮችን ሁሉ ላሳካለት ለእግዚአብሔር ከፍ ያለ ምስጋናውን አቅርቧል፡፡